Articles

May those with singular heritage raise their hand. ክፍል 2

በወጥ ማንነት መኖር ላይ ያለ ጥያቄ።
ክፍል ሁለት። የድብልቅ ማንነት እውነታ።
ባለፉት ውይይቶች ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ውሕድ ማንነት እንዳለን እና እንዴት አብዛኛው የአንድ ዘር
ማንነት አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ራቅ ስላሉት የዘር ቀደምቶቹ ያለው እውቀት እጅግ ያልተሟላ እንደሆነ
ተወያይተናል። የተሟላ መረጃ አለኝ የሚሉ እና እስከ ስድስትና ሰባት ትውልድ የሚቆጥሩ እንኳን
ከቀደምቶቻቸው ከ5% በታች ብቻ እንደሚጠሩ አይተናል። ስለሩቆቹ ይቅርና ስለቅርቦቹ ቀደምቶቻችንስ
እርግጠኛ ለመሆን የማንችልበት ምክንያት ምንድነው? በዚህ ጽሑፍ ይህንን ለማየት እንሞክር።
ሁሉም ሰው በትክክል እስክ አራት ቤቱ አባትና እናት፣ አያቶች የሚላቸውን ስማቸውንና ጎሳቸውን ያውቃል
እንበል። እናቱና አባቱን እርግጠኛ ቢሆን እንኳን ስለ አያቶቹ የእውነት በሥጋና በደም አያቶቹ መሆን እርግጠኛ
ሊሆን አይችልም። ለዚህ ጥርጣሬ ብዙ አሳማኝ መንሥኤዎች አሉት
1. ጉዲፈቻ። አንድ ሰው በጉዲፈቻ ሲያድግ ነገሩ በባህሉ የተደገፈና ምንም ምስጢርነት የሌለው ቢሆንም
ከአንድ ትውልድ በኋላ አንድ የልጅ ልጅ በቀጥታ አያቴ ይላል እንጂ የጉዲፈቻ አያቴ አይልም። ያለማቋረጥ
በሚደረጉት ጦርነቶች ምክንያት፣ ልጅም በጣም ተፈላጊ የነበረ በመሆኑም ምክንያት ጭምር ጉዲፈቻ
እጅግ በጣም የተስፋፋ ነበር። ዛሬ ስንት ሚሊዮኖች የጉዲፈቻ ተጠቃሚ ከነበረ የዘር ሐረግ እንደመጡ
አይታወቅም። በነገራችን ላይ ጉዲፈቻ በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ለሺዎች አመታት የተደረገ ነው።
ይሁን እንጂ ጉዲፈቻ ቃሉ ከኦሮምኛ የመጣ ( በአማርኛ ማደጎ ለሚባለው ባህላዊ ተግባር ትርጉም የሆነ)
በኦሮሞ ባህል ውስጥ በደንብ የዳበረና የተደነገገ ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል።
2. ውሸማ። በግልጽም ሆነ በስውር ውሽማ መያዝ በአንዳንድ ቦታ እንደ ነውር ባንዳንድ ቦታ እንደ ጀብዱ
የሚታይ እጅግ ተስፋፍቶ የኖረ ልማድ ነው። ከውሽማ የሚወለደው ልጅ ግን ስሙንና ዘሩን የሚቆጥረው
በሥጋ አባቱ ሳይሆን ከወላጅ እናቱ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ ባለው አሳዳጊ አባቱ በኩል ነው።
3. በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ባለትዳር ሴት ከሌላ ወንድ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት እንድታደርግ ባህሉ
ይፈቅድላታል። የሚወለደው ልጅ ግን በባሏ ዘር ሐረግ ይጠራል። ይህም የሚቆጥረው የዘር ሐረግ የሥጋና
ደም ወገኑን አያመለክትም ማለት ነው።
4. ጸንሶ መዳር። በተለያየ ምክንያት ሴቶች ከጸነሱ በኋላ (አንዳንዴ መጽነሳቸው ሳይታወቅ) ይዳራሉ።
የተጸነሰው ከሌላም ቢሆን ከተወለደ በኋላ በአሳዳጊ አባቱ ነው የሚጠራው። ዘሩንም በዚሁ ይቆጥራል።
5. ሕጻናት ይዛ ለሌላ የተዳረች፣ ብዙ ጊዜ ሕጻናቱ በአሳዳጊ አባታቸው ስም ይጠራሉ።
6. ጥቂት በማይባሉ አካባቢዎች ባሏ የሞተባትን ሴት ወንድሙ ይወርሳትና አዲስም የምትወልዳቸው ልጆች
በሞተው ባሏ ስም ይጠራሉ። በዘር ሐረግ አቆጣጠር ላይ ችግር የሚያመጣው የወለደችላቸው
ወንድማማቾቹ ያንድ አባት ልጆች በማይሆኑበት ጊዜ ነው።
7. ሌላው እጅግ ይዘወተር የነበረ ልማድ ልጆች በአያታቸው ቤት የሚያድጉበት ነው። በአያት ማደግ ብቻ
ሳይሆን ስማቸውም በአያታቸው ስለሚጠራ የዘር ቆጠራው ውስጥ ትልቁ የሥር ግንድ ተዘንጥሎ ይቀራል።
ለምሳሌ የእናት ወላጆች ጋር ካደጉ ያባታቸው የዘር ሐረግ ከቁጥሩ ሊወጣ ይችላል።
8. በስርቆት የተወለደ። በመደበኝነት ውሽማ ከመያዝ ውጭ ካላገቧት ሴት መሄድም የተነወረ ግን የተለመደ
ተግባር በመሆኑ የተወለደው ልጅ በአሳዳጊ አባቱ እየተጠራ ዘሩንም በዚሁ ይቆጥራል።
9. ጣልያን በሀገራችን ካስፋፋው ጊዜ ጀምሮ በሴትኛ አዳሪነት ከሚተዳደሩ ሴቶች የተወለዱ ከሚሊዮን
የማያንሱ ወገኖች አሉን። ጊዜውም ከሁለት ትውልድ በላይ ነው። የነዚህ ወገኖች ያባት የዘር ውርስ
ከየትኛው የኢትዮጵያ ነገድ፣ ጎሳ፣ ዘውግ፣ ብሔር መሆኑ አይታወቅም።
10.አስገድዶ በመድፈር — በሰላም ጊዜ። ይህ ድርጊት መታወቁ በሚያስከትለው አደጋ ምክንያት በሰላም ጊዜ
የተለመደ አይደለም የሚሉ ይኖራሉ። በተለይ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ። ይሁንና በሽፍትነት፣ በውንብድና እና
በአለሌነት ሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ሲያጋጥሙ፣ ውርደትን ለመሸፈን ጉዳትን መደበቅ የተለመደ
በመሆኑ የሚወለደው ልጅ በአሳዳጊ አባቱ እየተጠራ በዚሁ ዘሩን ይቆጥራል።
11.አስገድዶ መድፈር– በጦርነት ጊዜ።
ሀ. ከጦርነት እጅግ አስከፊው ገጽታ ይህ ነው ማለት ይቻላል። በዓለም በሙሉ የሚፈጸም አውሬያዊ
ወንጀል ነው። በዚህ ሁኔታ በእናት ላይ የሚፈርድም አይኖርም። ልጅም ከተወለደ የልጁ የሥጋ
አባት ያልሆነው የጋብቻ ባሏ እንኳን በጦርነቱ ቢገደል ብዙውን ጊዜ ስሙ በእርሱው በሟቹ አባቱ
ይጠራል። ዘሩም በዚሁ ይቆጠራል።
ለ. በጦርነት ጊዜ በጥንቱ ሥርዓት ወታደር በባላገር ላይ ይሠራል (ይመራል)። በየቤቱ ተከፋፍሎ
ይሰፍራል። የታጠቀው ወታደር መሣሪያውን በመመካት፣ ያላገባች ወይም ያገባችውን ሴት
የሚደፍርበት ጊዜ ብዙ ነው። በጎጃም የአጼ ዮሐንስ ሠራዊት በዚህ ነውር እጅግ ከመባለጉ የተነሳ
አፄ ዮሐንስ አልፈው በሚኒልክ ንግሥና ወቅት ያደጉ ልጆችን ብዙ ጊዜ “አንተ ይሄስ ሁለመናው
ያን ዘመን ተመርቶ የከረመውን ትግሬ ነው የሚመስለው” ማለት የተለመደ ነበር።
12.በዘመናዊ ጦርነት ወታደር ለረጅም ጊዜ በከተሞችና በአንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች ይሰፍራል። በወታደራዊ
አቋሙ፣ በአለባበሱም ይሁን በጀግንነቱ ሴቶች ወታደር መውደዳቸው የዓለም ታሪክ አካል ነው። በነዚህ
የጦር ሰፈሮች አቅራቢያ ብዙ ልጆች ከወታደሮች እንደሚወለዱ ስማቸው ግን ባሳዳጊያቸው እንደሚጠራ
ያደባባይ ምስጢር ነው። አንዳንድ ሰዎች ሰላሣ ዓመታት በዘለቀው ትግል ወደ ቤታቸው ያልተመለሱ
ታጋዮች ልጆች ግን እየተወለዱላቸው የነበረበትን ክሥተት ከጦሩ ጋር ከፍተኛ የዘር መደባለቅ
የተፈጠረበት ነበር ይላሉ። ጊዜው ሰላሣ ዓመት፣ ሰራዊቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠር መሆኑ ትኩረት የሚስብ
ያደርገዋል። ሁሉም አበሾች መሆናቸው እንጂ ሠራዊቱ ጣልያን ወይ አረብ ቢሆን የተከለሰውን ትውልድ
ብዛት በቀላሉ ለማየት ይቻል ነበር። ይሁንና አሁንም ፍላጎቱና ፈቃደኝነቱ ካለ ማወቅ ለሚፈልግ ዛሬ
ቴክኖሎጂው አለ።
13.ከላይ የተጠቀሱት (ውሸማ፣ ስርቆት፣ አስገድዶ መድፈር ወዘተ) ከትዳር ውጭ የመደራረስና
የመውለድ ነገሮች በሀገራችን የተጋነኑ አይደሉም ብለን ለምናስብ ሰዎች እንዴት በገጠር በከተማ አንድ
ትውልድ በኤይድስ እንደረገፈ ማስታወስ ይጠቅመናል። ካለበለዚያ ከዓለም በተለየ ሁኔታ እንደ ሰደድ
እሳት በኤይድስ የተፈጀንበትን ክስተት ለመግለጽ “ፈረንጆች የኤይድስን በሽታ በክትባት ወይም በሌላ
ቀጥተኛ ዘዴ አሰተላለፉብን” የሚለውን በስፋት የተሰራጨ መላ ምት መደገፍ ይኖርብናል። በሽታው ከታወቀበት ጊዜ በኋላ እንኳን በቀላሉ ሊቀነስ አለመቻሉ እንደ ቋያ እሳት ተዛምቶ እናትና አባትን
እስከልጆቻቸው የፈጀበት ፍጥነት ስለባህላችን ያለንን አመለካከት እንድንመረምረው የሚያደርግ ነው።
እነዚህ ለምሳሌ ያህል የተጠቀሱ ምክንያቶች ብቻ እንኳን ስለ ዘር ሐረጋችን በእርግጠኝነት ለመናገር እንዳማንችል
አመላካቾች ናቸው። ከእናትና አባታችን ውጭ የተቀረውን የዘር ሐረጋችን ሙሉ በሙሉ በእርጠኝነት መናገር
አንችልም።
ይበልጥ እናጥብበው ካልንም ከዲኤንኤ DNA መረጃ ውጭ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ስለናታችን
ብቻ ነው። ያውም እቤት ውስጥ ከተወለድን። ሆስፒታል ከተወለድን ላሳደጉን ወላጆቻችን የሌላ ወላጅ ልጅ
ተለውጦ ተሰጥቷቸው ሊሆን ሁሉ ይችላልና።
የጦርነትን ነገር ካነሳን አይቀር በጦርነት ጊዜ ከላይ ከተጠቀሱት ሌላም የዘር መቀላቀል የሚከሰትበት አጋጣሚ አለ።
ብዙ ጊዜ ከጦርነት የሚመለሰው ሠራዊት የገደለውን ገድሎ ያቃጠለውን አቃጥሎ የሰውና የንብረት ምርኮ ይዞ 3
ይመለሳል። በዚህ መሐከል ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነው ወጣት ተዋጊ ባሏ ወይም ወላጆቿ የሞቱባትን ያማረችውን
ወጣት ይዞ በመመለስ ጋብቻ ይመሰርታል። የታላቁ ደራሲ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ቤተሰብ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።
ከምኒልክ ንግሥና በኋላ በተነሳው የስልጣን ሽኩቻ የሸዋ ኦሮሞ ከወሎ ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ጦርነት ዝኆኖች
ሲዋጉ ሳሩ እንደሚጎዳው፣ የሰሜን ሸዋ አማራ ይወድማል፣ ቤቱ ይቃጠላል። በዚህ ጊዜ ከሞት የተረፉትን ሴቶች
የሜጫ ኦሮሞዎች ከድል መልስ ይዘዋቸው ወደ ምዕራብ ሸዋ ይመለሳሉ። የጸጋዬ ገብረመድኅን እናት እንዲህ
ሆነው መጥተው ለሜጫ ዘማቾች ከተዳሩ የአንኮበር ልጃገረዶች አንዷ ናት።
ባለፈው ጽሑፍ ከተጠቀሱት በርካታ የዉሑድ ትውልድ መንስኤዎች ሌሎች ብዙዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ
ያህል ግን የንግድ እንቅስቃሴን እንመልከት። በሀገራችን በቀደመው ዘመን የንግድ ሥራ ረጅም ጉዞን፣ በየከተማውና
ኬላውም ረጅም ቆይታን የሚጠይቅ ስለነበር ነጋዴዎች በተለይ ብዙ በሚቆዩባቸው ሰፈሮችና ከተሞች ከዋናው
ትዳራቸው ሌላ ትዳር መሥርተው፣ ቤት ሰርተው፣ ንብረት አፍርተው፣ ለመደብርና ለመጋዘናቸው ጠባቂ ያደርጉ
እንደነበር ይታወቃል። ሁሉም ያደርገው የነበረ ቢሆንም በተለይ በእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን ዘንድ
ሃይማኖቱም ስለማይከለክል ከአካባቢው ተወላጅ ጋር ሕጋዊ ትዳር መሥረተው ልጆች ያፈሩ ነበር። ሃይማኖቱ
ቢከለክልም ጥቂት የማይባሉ ክርስትያን ነጋዴዎችም ሆኑ ከቦታ ቦታ እየተቀየሩ የሚሠሩ የጦር አበጋዞች የዚህ
ልማድ ተሳታፊዎች ነበሩ።
ባለፉት ሦስት መንግሥታት ዘመን ደግሞ የሹፌርነት ሙያ ለዘር መቀላቀል አስተዋጽኦ አድርጓል። ራሳቸው
ከተለያዩ ብሔር የሆኑት እና በረጅም ጉዞ ብዙ ቀናትን የሚያሳልፉት በተጨማሪም ሀገሪቷን ከጥግ ጥግ
የሚያዳርሱት ሹፌሮች፣ በጋብቻ፣ በውሽምነት ና በአዳር ቆይታዎች ከኢትዮጵያ የተለያዩ ዘውጎች ዘራቸውን
ቀላቅለዋል።
ሌላው እጅግ ተስፋፍቶ ለዘመናት የኖረው የባርያ እና የባርነት ሥርዓት ነው። ባርነት እጅግ አስከፊ ሥርዓት መሆኑ
ባይካድም ከአሜሪካና እንግሊዝ የባርነት ሥርዓት በተለየ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአገልጋይ/ባርያ የተወለዱ ብዙ ሰዎች
ከደጃዝማችነትና ራስነት አልፈው በንግሥና ሀገራችንን እስከመምራት ደርሰዋል። እጅግ ብዙ ስለሆኑ መጥቀስ
አስፈላጊም አይደለም። ፈረንጆች ከባርያቸው የወለዷቸውን ልጆች ይሸጧቸው ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ባርነት
በቀለም ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ባሸናፊና በተሸናፊነት ላይ የተመሰረተ ስለነበር የባርያ ሥርዓት ሲወገድ ዛሬ ማን
በዘሩ ባርያ / አገልጋይ የነበሩ ቀደምት እንዳሉበት ለማወቅ አይቻልም። በዚህም ባርያ ሆኖ የመፈንገል ወይም
የማገልገል የወር ተራ ያልደረሰው የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረም። በጦርነት ከመሸነፍ ሌላ ባርነት በችግር ምክንያት በፈቃደኝነት፣ እና በእዳ ምክንያት በግዴታ የሚከሰት ነበርና ከዚህ ያመለጠ ሕዝብ አይገኝም። ከዳር እዳር የዘር መደባለቅን የፈጠረው የጦርነት-ወለዱ ባርነት ጉዳይ ግልጽና የታወቀ ስለሆነ በፈቃደኝነት ይደረግ ስለነበረው ባርነት ብቻ ምሳሌ ጠቅሰን እንለፍ።
በጉራጌ አገር በሰሜን ኢትዮጵያ ከተለመደው የእህልና ጥራጥሬ ሰብል በተጨማሪ የእንሰት አዝመራ በሰፊው
ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህም ምክንያት በምሥራቅ አፍሪካ አዘውትሮ የሚከሰተው ድርቅ የአመትና የሁለት
አመት ዝናብ ሲከለክል በጉራጌ አገር ረሃብ አይገባም። ምክንያቱም ከሰባት እና ስምንት አመታት ጀምሮ የበቀለው
እንሰት አዝመራው በምግብነት ስለሚያገለግል ነው። ዙሪያውን ያለው ሕዝብ ግን እንደቅጠል ይረግፋል። በዚህ
ጊዜ በጉራጌ አካባቢ ካለው ሕዝብ እንደ ወሊሶ፣ አመያ፣ ጊቤ ካሉት አካባቢዎች በድርቁ ብርታት እየተጠቁ ሙሉ
ቤተሰብ ከማለቅ በሚል አንድ ወጣት ልጃቸውን ጉራጌ አገር ወስደው ለባርነት/አገልጋይነት ሰጥተው በለውጡ
ውሳ (የእንሰት ምርት) ጭነው በመመለስ ሕይወታቸውን እና የልጆቻቸውን ሕይወት ያተርፉ ነበር። እነዚህ
“የተሸጡ” ወጣቶች ታድያ ታታሪና ተግባቢ ሆነው በዚያው ተድረው የሚቀሩበት ጊዜ ብዙ ነበር። በዛውም ልክ
ዝናሙ ሲመለስ የአመታት አገልግሎታቸውን ጨርሰው፣ ወይም ዕዳቸው ከፍለው የጉራጌ ሙሽሪት ይዘው ወደ
ትውልድ ቀዬአቸው የሚመለሱም ብዙ ነበሩ። በዚህ ምክንያት የተደባለቀውን የሸዋ ዘር ልክ ለመገመት ያዳግታል።
የዘር ቆጠራ ነገር እና የጉራጌ አገር ከተነሳ በጉራጌ እጅግ ብዙ ቤተሰቦች አሥራ አራት ትውልድ ድረስ ይቆጥራሉ።
አሥራ አራት ትውልድ ቆጥረው ከኤርትራ ጉርዐ በጦር አዝማችነት ከመጡት ወታደሮች ቀደምቶቻቸው
ይደርሳሉ። ይህ ግን የጠራ ዘር ምልከት ሆኖ እንዳያሳስተን ጥንቃቄ ያሻል። ቆጠራው በወንድ ዘር ሐረግ አንዱን
ቅርንጫፍ ብቻ እየተከተለ የሚወጣ ስለሆነ ከ2
14 = 16384 ። እንግዲህ ይህ አሥራ አራት ትውልድ ዘር ቆጠራ እጅግ አስደማሚ ቢሆንም ከ 16384 ቀደምቶች ስለ አንዱ ብቻ ነው የምናውቀው። ከየት እንደመጡ የምን ጎሳ እንደሆኑ የማናውቃቸው 16383 አሥራ አራተኛ ትውልድ ቀደምቶች አሉን ማለት ነው። የምናውቀው አንዱን
ነው። በጄኔቲክስ (የዘረመል) ትምህርት ደግሞ ከዚህ አንድ ቀደምት ለኛ የሚደርሰን የዘር ክፍያ ሲሰላ ከዘር
ውርሳችን (ከኛ DNA) 0.001 %ያህል ብቻ ነው። ከዚህ ከአንዱ አሥራ አራተኛ ቀደምታችን የወረስነው ይህ
ብቻ ነው። ሌላው የዘር ውርሳችን ስማቸውን እንኳን ከማናውቀው ከ 16383ቱ የተሰጠን ነው። በሌላ በኩል
የሚታወሰን ደግሞ እነዚህ 16384 ቀደምቶች ከእኛም ሌላ በመቶሺህ ለሚቆጠሩ ሌሎች ኢትዮጵውያውያን “ወላጅ
ቀደምቶች” መሆናቸውን ነው።
ከጉርዐ የመጡት ወታደሮች ዘማች ሆነው ሲመጡ ምናልባት ሴቶቹን ከአካባቢው ተወላጅ አግብተው ሊሆን
ይችላል። የእንሰቱና የእህል ጥራጥሬው አመጋገብ ጥምረት ይህንን ጠቋሚ ነው። የበጌምድር የደምቢያ ሰዎች ወደ
ኤርትራ (ሐማሴን፣ አካለ ጉዛይ እና ሰራዬ) ከዛሬዋ ኤርትራ ደግሞ የጉራጌ፣ የሥልጤ፣ የአርጎባ እና የአደሬ
(ሀረሪ) ቀደምቶች ወደ መሀል አገር የመጡበት ዘመን በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ እጅግም ጥንት የሚባል አይደለም።
ከዚያ በፊትስ ስንት መቀላቀል ተክስቶ ይሆን? ከዚያ ወዲህስ ስንት?
ዛሬ ከኦጋዴን ኦሮሞ ተብለው የተባረሩት ጃርሶዎች በኦሮሞ የተዋጡ የሱማሌ ጎሳ ነበሩ። የቦረና ወረራ ወደ
ሰሜንና ወደ ምእራብ ኢትዮጵያ በዘለቀ ዘመን ጃርሶ በሌላኛው የኦሮሞ ክንፍ በበሬንቱማ ተወርረው በሬንቱማ
የተደረጉ የሱማሌ ነገድ ነበሩ። የክልል ፖለቲካ ሰለባ ሆነው ካባቶቻቸው ቀዬ በደም ወንድሞቻቸው ተባርረዋል።
ሱማሌነቱም የነርሱ ኦሮሞነቱም የነርሱ። የመረጡት ሳይሆን ታሪክ የሰጣቸው። በደማቸው ያለውን ማን
ሊነጥቃቸው ይችላል?
በክፍል ሦስት እንገኛኝ
በቸር ይግጠመን።
ዘአብ አሉበ
#ውሕድ ኢትዮጵያዊ ገፅን Like ያድርጉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *