Articles

የውሕድ ማንነት እውነታ/በወጥ ማንነት መኖር ላይ ያለ ጥያቄ/ የክልል ሥርዓት በውሕድ ማንነት ላይ የደቀነው አደጋ። ክፍል 1

እጃችሁን አውጡ (May those with a singlular heritage stand up)
ዉሑድ መሆናችሁ እንዲጣራላችሁ
እስኪ እጃችሁ ይውጣ ውሕድ ያልሆናችሁ
በእናት ባባታችሁ ምንም ሳታስቀሩ
እስኪ ስምንት ቤት ዘር ሐረግ ቁጠሩ
እሺ ስምንት ይቅር በጣምም አትልፉ
እስከ ምንዝላቶች የወንድ የሴት ጻፉ
በሉ ይቺን ቁጥር ባንድ ላይ እንያት
የእናት ያባታችሁ አራት አራት አያት
የአራት አያቶች አስራ ስድስት አያት
የእኒህ ሰላሣውን እንኳን ዘራቸውን
እውነት ታውቃላችሁ ሙሉ ስማቸውን?
የነሱ ወላጆች ምንዝላት ያሏቸው
ወንድና ሴቶቹ ሰላሣ ሁለት ናቸው
እነዚህ ቀደምቶች ሁሉም ስልሳዎቹ
ካንድ ጎሣ ለማለት ለወሬ አይመቹ።
ስለዚህ እናንተም ባልወጣው እጃችሁ ባ
ታውቁት ነው እንጂ ዉሑድ ዜጋ ናችሁ።
(ምንዝላት = 5ኛ ቤት)
(አያት፣ ቅድመ አያት፣ ቅምቅማት፣ ምንዝላት፣እንጅላት ወይም እንጅልሽ የሚለው አንዱ የቀደምት አሰያየም ነው።)
ወገኔ ሆይ!
ሁለት ወላጅ አለህ — 2
አራት አያት አለህ — 4
ስምንት ቅማት አለህ — 8
አስራ ስድስት ቅምቅማት አለህ — 16
ሰላሳ ሁለት ምንዝላት አለህ — 32
ስልሣ አራት እንጅልሽ አለህ — 64
መቶ ሃያ ስምንት ምናውቅልሽ አለህ — 128
ስምንት ቤት ብትቆጥር — 256
ሲደመሩ 2 + 4 + 8 + 16 + 32 + 64 + 128 + 256 = 510
የእነዚህን 510 ሰዎች ይቅርና ጎሳቸውን – ሙሉ ስማቸውን እንኳን – (ከተራው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ቀርቶ ታሪካቸው በስፋት ተመዝግቦ ከሚገኙት የንጉሳውያን ቤተሰቦችም መካከል) ወደ ኋላ አምስት መቶ አስሩንም የሚቆጥሩ፣ ወይም የተጻፈላቸው የሉም።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ብንወስድ የሁለቱ ኦሮሞ ወንድ አያቶቻቸው ስም የታወቀ ሲሆን ከሴት አያቶቻቸው የሳባ ንጉሣዊ ዘር የሆኑት የአንዷ ብቻ በእርግጠኝነት ይታወቃል። የዳግማዊ ምኒልክ አያቶችን በተመለከተ የመረጃው ክፍተት ከዚህም የባሰ ነው።
ይሄንን የእውቀት ጉድለት፣ የመረጃ ክፍተት፣ ይዞ የጠራሁ ቦረና ነኝ፣ የጠራሁ መንዜ ነኝ፣ የጠራሁ ሲዳማ ነኝ ማለት ካለማወቅ ወይም ከማፌዝ ካልሆነ በስተቀር ከምር ሊሆን አይችልም።
የጠራሁ ኦሮሞ፣ የጠራሁ ጎጃሜ፣ የጠራሁ ወሎዬ፣ የጠራሁ ትግሬ የሚሉት አባባሎች ቀልድና አስቂኝ ለመሆናቸው የኦሮሞን ታሪክ የጎጃምን ታሪክ የወሎን ታሪክ፣ የትግሬን ታሪክ የሩቁን ሳይሆን የቅርቡን ብቻ ማወቅ በቂ ነው።
ኦሮሞ የጋፋት፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣የዳሞት፣ የቢዘም፣ የሃዲያ፣ የጉራጌ፣ የማያ፣ የባሊ፣ የሶማል፣ የአፋር ሕዝቦችን በደም ሥሩ ያቀፈ ማንነት ነው።
ጎጃም የጋፋት፣ የዳሞት፣ የቢዘም፣ የአገው፣ የኦሮሞ፣ የሽናሻ፣ የሻንቅላ፣ የጉምዝ፣ የአማራ ደም በውስጡ ያቀፈ ነው። ወሎ የአገው፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የትግሬ፣ የአማራ፣ የአርጎባ፣ ደም ያለበት ማንነት ነው።
ትግሬ የባርያ፣ የኩናማ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኢሮብ/ሳሆ፣ የአሳውርታ፣ የቤጃ፣ የትግሬ፣ የዋጅራት፣ የአፋር ደም ያለበት ማንነት ነው።
ምኑ ነው የጠራው? ከምንድነው የሚጠራው?የጠራሁ የቻይና ወይም የናይጄሪያ ዘር የሌለብኝ ጎጃሜ፣ ኦሮሞ፣ ወሎዬ ወይም ትግሬ ነኝ ለማለት ከሆነ ያስኬዳል።
ከላይ በቆጠርናቸው 510 የስምንት ቤት ብቻ ቀደምቶቻችን ውስጥ ሰማንያዎቹ የኢትዮጵያ ነገዶች ብቻ ሳይሆኑ ሌላም ከመቶ በላይ ጎሳዎች ሊካተቡበት የሚችሉ ሰፊ ቁጥር ነው።
እንግዲህ ጦርነትና የሕዝቦች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ለአንዳፍታ እንኳን ባልተለያት ሀገራችን ውስጥ እንዴት አንድ ሰው በስምንት ትውልድና በ510 ቀደምቶቹ ውስጥ ሌሎች ጎሳዎች ያልተካተቱበት ወጥ ማንነት አለኝ ብሎ ሊያስብ ይችላል?ደሜ ከአንድ ጎሳ፣ ዘውግ፣ ነገድ ብቻ የተቀዳ ነው ማለት እውነትነት ይኖረዋል?
ይህ አጋጣሚ የመከሰት እድሉ እጅግ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በሂሳብ ቢሰላ ከመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ስምንት ቤቱ ወጥ አንድ ጎሳ የሆነ አንዲ ሺህም ሰው ላይገኝ ይችላል። የኔ ግምት ነው።
አንድ ሰው ምንም ያልተቀላቀለ የጎሳ፣ የዘውግ ወይም የነገድ ማንነት አለኝ ካለ መብቱ ነው። አባባሉን በሐቅ ለማስደገፍ ግን እጅግ አዳጋች ይሆንበታል።
ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ከሰሜኑ ኢትዮጵያ እየተነሱ ደቡቡን ክፍል የወረሩ፣ ያስገበሩ ነገሥታት ሠራዊታቸውን ይዘው ከመዝመትም ሌላ በነዚሁ ቦታዎች ሠራዊት ያሰፍሩ ነበር። ይህም እስከ አጼ ምኒልክ ጊዜ የቀጠለ ነበር። ለሺዎች ዓመታት አልፎ አልፎ ጋብ እያለ የቀጠለ ታሪክ ነበር።
ሰሜናዊ ዘርን ከናቅፋ እስከ ከፋ የዘራ ክስተት ነበር። ግራኝ የሱማሌ፣ የሐረሪ እና የአፋርን ጦር መርቶ ድፍን ኢትዮጵያን ሲያጥለቀልቅ የሱማሌ፣ አፋርና፣ ሐረሪ ዘር በድፍን ኢትዮጵያ ከበርበራ እስከ ወንበራ መሰራጨቱ አይቀሬ ነበር።
ከግራኝ በኋላ ቦረና እና በሬንቱማ ወደ ሰሜን ያደረጉት ከመቶ ዓመታት በላይ የዘለቀ ወረራም የኢትዮጵያን ከግማሽ በላይ የሚሆን መሬት የዳሰሰ ስለሆነ የኦሮሞ ዘር በስፋት ከሞያሌ እስከ አበርገሌ የተሰራጨበት ክስተት ነበር።
እነዚህም ወራሪዎች ወርረው የተመለሱ ሳይሆን በብዛት ሰፍረው ሀገሬ ሆነው የቀሩ ናቸው።
የደርግም ሦስት መቶ ሺህ ሚሊሺያ እና ሌሎች ብዙ መቶ ሺህ መደበኛ ሠራዊቶች በአሥራ ሰባቱ ዓመታት ከድፍን ኢትዮጵያ ተውጣጥተው በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭተው ዘር ማፍራታቸው ለሚሊዮኖች ዘር መደባለቅ እድል የፈጠረ ክስተት ነበር።
እነዚህ ጥቂት ታላላቅ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች የተጠቀሱት ስእሉን ለማሳየት ያህል እንጂ ለሺህ ዘመናት በሕጋዊ ጋብቻ፣በባርነት፣ በጠለፋ፣ በምርኮ፣ በፍልሰት፣ በሞጋሳ፣ በጉዲፈቻ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ሌሎችም ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘር ማንነት የተደበላለቀበትን መጠን ለመገመት እጅግ አዳጋች ነው።
እስልምና እና ክርስትና በስፋት ተስፋፍተው ይገኛሉ። እነዚህ ሃይማኖቶች የተስፋፉበት መንገድ ራሱ አንድ የዘር መደባለቅን የሚፈጥር ክስተት እንደነበር መካድ አይቻልም።
የጥንቱም ሆነ ዘመናዊው ትምህርት የተስፋፉት ከተለያዩ ቦታዎች ተነስተው ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄደው ተምረው ከዚያም በድፍን ኢትዮጵያ ተበትነው ባስተማሩ መምህራን ነው። እነዚህም በየሄዱበት ከሃገሬው ተወላጅ ጋር ጋብቻ እንደፈጸሙ እሙን ነው። እኔ ራሴ ሸዋ ተወልጄ አድጌ የትግራይ፣ የሐማሴን የወላይታ እና የወለጋ ተወላጅ መምህራን ነበሩኝ። አንዳቸውም ወደ ትውልድ ቦታቸው የትዳር ጓደኛ ፍለጋ አልተመለሱም። እንዲያውም ብዙዎቹ ከተማሪዎቻቸው መሀከል ነው የትዳር ጓደኛ የመረጡት።
ከ510 ቀደምቶቻቸው ይቅርና እናት እና አባታቸው፣ ወይም አራቱ አያቶቻቸው ከተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦች እንደመጡ የሚያውቁና የሚቀበሉ ሰዎች ዛሬ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተጫነው ስርዓት ዜግነትም ሆነ ነጻነት የላቸውም። መግቢያ የሚያገኙት፣ መግቢያ ካገኙ፡ የተወሰነውን ማንነታቸውን ክደው ነው።
ማንነትን ለማጎልበት በሚል ማጭበርበርያ የተጫነብን ሥርዓት በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማንነት የሚደፈጥጥ ነው። የነርሱን የዛሬ እድል ማጨለም ብቻ ሳይሆን የተቀሩትንም (ዛሬ መግቢያ አለን ያሉትንም) የልጆቻቸውን እድልና የራሳቸውንም ነጻነት ገፋፊ ሥርዓት ነው።
ለምሳሌ ሱማሌ ነኝ ብላ የምታምን ሴት ኦሮሞ ነኝ ብሎ ከሚያምን ወንድ ጋር ትዳር መሥርታ ልጆች ታፈራለች። እርሷም እርሱም ማንነታቸውን የሚያከብሩ ክልሎች አሏቸው/ነበሯቸው እንበል። የወለዷቸው ልጆች ግን ክልል አልባ ናቸው።
ሥርዓቱ በዚህ ዓይነት የልጆቼ እጣ ፈንታ ምን ይሆን በማለት ገና ያልተወለዱ ልጆቻቸው አገር አልባ፣ እና ነጻነታቸው የተገፈፈ እንዳይሆኑ በመፍራት የወደዱትን ወይም የመረጡትን ሌላ ኢትዮጵያዊ ከማግባት ተቆጥበው በክልል አጥር ውስጥ የታገዱ እና በዚህ ረገድ ነጻነታቸው የሚገፈፍ ባለክልል ሚሊዮኖችንም ፈጥሯል።
ዛሬ ከሰላሣ ዓመት እድሜ በላይ ከሚገኘው ከወያኔ በፊት በተወለደው በአርሲ፣ በሸዋ፣ በወለጋ ኦሮሞ ውስጥ ከአራቱ አያቶቹ አማራ ያለበትን ከመቁጠር የሌለበትን መቁጠር እጅግ ቀላል ሥራ ነው።
ከጎጃም ከወሎ ከሸዋ አማራ ውስጥ ደግሞ ኦሮሞ ያለበትን ከመቁጠር የሌለበትን መቁጠር ቀላል ስራ ይሆናል። የሌለበት ከተገኘ እጅግ ጥቂት ስለሚሆን።
የክልል ሥርዓት አንዱ መጥፎ ገጽታው አሸባሪ መሆኑ ስለሆነ ሰዎች የወላጆቻቸውን ወይም የአያቶቻቸውን ዘውግ ለመደበቅ ይገደዳሉ። ማንነትህን የማይቀበል፣ የሥራ ቅጥር፣ የፖለቲካ ነጻነት፣ በወላጆችህ ቋንቋ የመማር፣ እና ሌላም የዜግነት ነጻነት የሚገፍህ ስለሆነ ተሸብረህ የምትኖርበት፣ ክደህ፣ ለሌሎች ሰግደህ የምትቀመጥበት ሁኔታ መፍጠሩን ነው አሸባሪ የምንለው።
ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ እንዲህ ዓይነት ዘር እንዳለባችሁ አትናገሩ የሚሉበት ሕይወት የሽብር ሕይወት ነው። በደርግ ጊዜ የሃብታም ልጅ ነኝ አትበሉ፣ መሬት ነበረን አትበሉ፣ ቤት ነበረን አትበሉ፣ የባላባት ዘር ነን አትበሉ፣ ዘር ማንዘሬ ጭቁን፣ ያጣ የነጣ ደሃ ነው ብቻ በሉ እየተባለ በሽብር የሚኖሩ ሸራፋ ዜግነት የተሰጣቸው ብዙ ነበሩ። በክልል ሥርዓት ደግሞ እንደ ክልሉ፣ ኦሮሞም ነኝ፣ ሶማልም ነኝ፣ አማራም ነኝ፣ ትግሬም ነኝ አትበሉ፥ ሌላ ዘር እንዳለባችሁ አትናገሩ እየተባሉ የሚያድጉ ሚሊዮን ተሸባሪዎች ተፈጥረዋል።
ይህ የመብት ረገጣ ብቻ ሳይሆን በስነ ልቡናዊ ጭንቀት የጤና ችግር ሊፈጥር የሚችል አደገኛ ግፍ ነው።
እስኪ ለምሳሌ እናቴ ኦሮሞ ናት አባቴ ትግሬ ነው እንበል። የእናቴን ዘር ክጄ በትግርኛ ብቻ እንድማር ብደረግ እንዴት ነው ማንነቴ የሚበለጽገው? ወይም አባቴ መንዜ ሆኖ እናቴ ሶማሌ ብትሆንና ኦጋዴን ውስጥ በተሟላ ዜግነት ለመኖር ያባቴን ዘር ክጄ በሶማልኛ ብቻ ተምሬ፣ ሶማል ብቻ ሆኜ መኖር ብገደድ ማንነቴን አበለጸግኩት ማለት ነው?
ይህ የክልል ሥርዓት ወደ ኋላ ሄዶ የቀደሙትን ወላጆቻችንን፣ ዛሬ ላይ የኛን፣ ነገ ደግሞ የልጆቻችንን ማንነት የሚገፍ፣ የሚደፈጥጥ፣ የሚሰርዝ፣ የሚደልዝ፣ የሚከለክል አሸባሪ ሥርዓት ነው። ትናንትን ዛሬን እና ነገን የሚበድል ልዩ የጭቆና ሥርዓት ነው ማለት ነው። ይዘገንናል።
ሰው ዛሬ ተበድሎ ለነገ ያልፍልኛል ወይም ለልጆቼ ያልፍላቸዋል ብሎ የሚኖርባቸው አስከፊ ሥርዓቶች አሉ። ነገን ይበልጥ በሚያጨልም ሥርዓት ዛሬ ልጨቆን የሚል ሰው ግን አይኖርም።
ዘአብ አሉበ (Ze’ab Alube) ፣ 2011

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *