የሚድያው ዋና ሃሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ነጻነት ለማክበር በሚል የተተከለው ሥርዓት በአወቃቀርም ሆነ በአፈጻጸም የሚሊዮኖችን የብሔር ነጻነት የማያከብር መሆኑን ለማስተማር ነው። የተተከለው ሥርዓት ከነጉድለቶቹም ቢሆን እቆማለሁ የሚልለት ዓላማ በትክክል ቢተገበር እንኳን መብታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚነፍጋቸው ሚሊዮናት ኢትዮጵያውያን አሉ። ወደፊትም ይኖራሉ። እነዚህም ከሁለትና ከዚያም በላይ ከሆኑ ብሔሮች የተወለዱ ዜጎች (ውሕድ ማንነት ያላቸው) በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ከተለያየ ነጠላ ማንነት ካላቸው ብሔሮች ተገኝተው ከእነሱ ብሔር ውጭ ትዳር የመሠረቱ ወይም የሚመሠርቱና ውሕድ ማንነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚወልዱ ናቸው። ይህ ማለት እጅግ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለከት ጉዳይ ነው። ክልሎች ለ“ጠ” ብሔር ወይም ለ“ጨ” ብሔር ተለይተው ሲሰጡ፣ ከ”ጠ“ እና ከ“ጨ” ብሔሮች የተወለዱ ግን ከሁለቱም የተነቀሉ፣ ወይም አንደኛው ማንነታቸው ተጨፍልቆ እንዲኖሩ የተገደዱ ይሆናሉ። ይህም በከፍተኛ ሽብር የታጀበ (መነቀልን፣ ቤት ንብረት፣ ሠርቶ የመኖር እድልን መነፈግን፣ መገለልን የማስከተል ባሕርይ ያለው)በመሆኑ ማንነትን በመደበቅ ወይም በመጨፍለቅ አንደኛውን ብቻ መርጦ መጓዝን ያስከትላል። ይህ ደግሞ የማንነት ቀውስ የመፍጠር ትልቅ እድል አለው። በስፋትም የታየ ነው። ባለ ጊዜ የሆነውን ማንነታቸውን መርጠው ከቄሱ በላይ ጳጳስ ለመምሰል በሚያደርጉት ሩጫ የጭካኔ እና የክፋት ጥግ ሆነው የተከሰቱ ውሕድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ምሳሌዎች ከደደቢት እስከሚኔሶታ በሽበሽ ናቸው። የሰዎችን የብሔር መብት ለማክበር የተደረገው ትግል መቋጫ፣ የብሔር መብትን በመጨፍለቅ ተጠናቀቀ የሚያስብል መደምደሚያ ነው የፈጠረው።
ውሕድ ማንነት ባለፈው ታሪካችን የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን የዛሬው ታሪካችን እና የነገውም እየፈጠረው የሚሄድ እንደመሆኑ ዛሬ ውሕድ ማንነት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ዛሬ ከአንድ ብሔር ነው የተገኘሁት የሚሉ ሰዎችንም መብት የሚጋፋ (ከሌላ ብሔር የሚወልዷቸው ልጆቻቸው የእነሱን ወይም የሌላውን ወላጅ እንዲክዱ የሚያስገድድ ሥርዓት)ነውና ሁሉም ይህን ጉድለቱን እና የሚያደርሰውን በደል ሊረዳ ይገባል። አፓርታይዳዊ የብሔር ሥርዓት በመሠረቱ ትናንትን ዛሬንና ነገን የሚበድል በዓለም ላይ እጅግ የተለየና የከፋ የጭቆና ሥርዓት ነው። የሰዎችን መብት ለማስከበር የሚተጋ ሁሉ መብት በማክበር ስም የሌሎች መብት እንዲጨፈለቅ አይፈልግምና ያለፉት ሰላሣ አመታት ቋንቋና ብሔርን መሠረት ተደርገው የወጡት ጨፍላቂ የአስተዳደር ፈሊጦች የፈጠሩትን ችግር በወደፊትም የሕብረተሰቡ ሕይወት ላይ የደቀኑትን አደጋ በትምህርት መልክ ለሕብረተሰቡ ማስገንዘብ የውሕድ ኢትዮጵያዊ ሚድያ አንዱ ዓላማ ነው።
ለዚህም በመጀመሪያ ውሕድ ማንነት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ምን ያህልስ የሕብረተሰቡን ክፍል እንደሚሸፍን ለማወቅና ለማሳወቅ ይሞከራል። ከታሪክ አኳያም ታሪካችን በዘመናችን ለተከሠተው ግዙፍ ውሕድ ማንነት ያለው ሕብረተሰብ መፈጠር ምን አስተዋጽኦ እንደነበረው ለማስረዳት ይሞከራል። ዛሬ ደግሞ ከሕግና ከፖለቲካ ጉዳዮች አኳያ የሚፈጠሩ የመብት መገደቦችና ሌሎችም እክሎች ምን እንደሆኑ ይፈተሹበታል። የታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ምሑራን ሰዎች እይታም ይደመጥበታል።
ለበለጠ ማብራሪያ ባለፈው አንድ ዓመት የተሠሩትን ፕሮግራሞችና በፌስ ቡክ እና መረጃ ቲቪ ላይ በውሕድ ኢትዮጵያዊነት ርእስ ላይ የቀረቡ አጫጭር ጽሑፎች ይዘት ይመረምሩ ዘንድ ይመከራል።