አማራ ነኝ ያውም ኦሮሞ
ጉራጌ ነኝ ያውም ሲዳሞ
ሱማሌ ነኝ ያውም ከትግሬ
ከደቡብ ነኝ ያውም ሃረሬ …
ከአፋር ነኝ ያውም ጋምቤላ
ከስልጤ ነኝ ውስጤ ሲሰላ
በዚህ መለኪያ – ሁልግዜ ‘ምገኝ
የዘሬ አርማዬ – ደምቆ ሚታየኝ
ኢትዮጵያዊነት – ‘ያንቆጠቆጠኝ
ውህድነቴን – ማነው ‘ሚነጥቀኝ ?
ኸረ ማንም !
ደሜ ተሳስሮ – አንድ ሆኜ ‘ምገኝ
መደራጀቱ – ለምን ሊጠቅመኝ ?
ዘሬ ተሳስሮ – በውህድ ሜዳ
ተለያይቼ – ለምን ልጎዳ ?
በእናት ባባቴ – የተጣመርኩኝ
የኢትዮጵያን ሞገስ – የተሸለምኩኝ
ዘር እማልቆጥር – የመሰረቴን
በኢትዮጵያ መሬት – ያኖርኩ እትብቴን
ጠንካራ መንፈስ – የማልደፈር
ባገሬ ሰማይ – ከፍ ብዬ ‘ምበር
በዘር ማልኮራ – ጎሳን ማልጠራ
በሰብአዊነት – ቤቴን ‘ምሰራ
በማህበሩ – የተዋሃድኩኝ
በአጋፔ ማዕድ – ውስጤን ያተምኩኝ
ዘር ‘ማልቆጥር – በሁሉም ቦታ
በየሄድኩበት – ጥልን ‘ምረታ
የትውልድ ብሶት – የሚያስጨንቀኝ
ስለ አንድነት – ዘወትር ‘ምቀኝ
ወንጌል ‘ምዘራ – በእሾህ ልብ ላይ
በጥረቴ ልክ – ለም መሬት የማይ
በእናት ባባቴ – የተዋሃድኩኝ
ታላቅ ሃገርን – የተሸለምኩኝ …
እናንተስ 
© ከናቲ ቪሎፒያ (ጋዜፀሃዲዛ)
